በመጭው የክረምት ወራት የበጎ ፍቃድ ተግባርን በበቂ ሁኔታ ለማከናወን የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የባህርዳር ከተማ ሴቶች ህፃናት ወጣቶች መምሪያ አስታወቀ።
"በጎነት ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ በ2013 የሚከናወነው የክረምት ወራት በጎ ፍቃድ ንቅናቄ እንደ ከተማ በ40 ቀበሌዎች የሚገኙ በጎ ፍቃደኞች ጊዜዓቸውን፣ጉልበታቸውን፣ገንዘባቸውን፣እውቀታቸውን በአካባቢና ማህበረሰብ ልማት ላይ እንዲሳተፉ የሚያስችል ስርዓት መቀመጡንና የሚሰሩ ዋና ዋና ተግባራት እስከ አፈፃፀም ሂደቱ ተለይቶ በሚመለከታቸው ባለሙያዎች ለቴክኒክና ስትሪንግ ኮሚቴው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
በባህርዳር ከተማ አስተዳደር ብልፅግና ጽ/ቤት የህዝብ ተሳትፎ አደረጃጀት አማካሪ አቶ በሪሁን መንግስቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት እየተለመደ ከመምጣቱ ባሻገር በርካታ ወጣቶች በጉጉት የሚጠብቁት ተግባር ቢሆንም እንደ ከተማ ሲታይ ግን ተፈላጊውን ውጤት በማምጣት በኩል የሚታዩ ክፍተቶችን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል።
የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ አምሳል ካሳው የክረምት በጎ ፍቃድ ውጤታማነት የሚገለፀው በቅንጅት ሲፈፀም መሆኑን አንስተው በከተማና ገጠር ባሉ 40 ቀበሌዎች ከ112ሺ 5መቶ በላይ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማሳተፍ ለህዝባችን ውጤታማ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አበርክቶ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
በዚህ የክረምት ወቅት ከተለመዱ የአካባቢና ማህበራዊ ልማቶች በተጨማሪ "አሁንም ትኩረት ለወጣቶች "በሚል ጽንሰ ሀሳብ ምክኒያታዊ ወጣቶችን ከማፍራት፣ወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ጋር በማቀናጀት የሚከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
የ2013 ዓ/ም የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከሐምሌ 01 እስከ ነሐሴ 30 የሚከናወን ሲሆን የመዝጊያና ማጠቃለያ ፕሮግራም ጳጉሜ ላይ እንደሚሆን ተገልጿል።