ሐምሌ 06/2013
በባህርዳር ከተማ አስተዳደር በ2 ዋና ዋና መንገዶች ላይ የትራፊክ መብራቶችን ሊሰራ መሆኑን የትራንስፖርት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡
============================
በከተማችን ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሸከርካሪ ቁጥር ከመጨመሩ የተነሳ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ እያስከተለ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ በቀላል የሚገመት ባለመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ከመቸውም ጊዜ በላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡
የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ስንታየሁ ዘለቀ እንደገለጹት እንደ ባህርዳር ከተማ በዚህ በጀት ዓመት የከፋ ችግር ባለባቸው የተባበሩትና መነሐሪያ አካባቢ 2 የትራፊክ መብራቶችን ለመትከል በታቀደው መሰረት 2ቱም ተሰርተው ውጤታማ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጅ አሁንም በተለየ መልኩ የትራፊክ ፍሰቱ እየጨመረ በመምጣቱና ከሰው ኃይል ቁጥጥር በላይ በመሆኑ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ በርካታ ጉዳቶች እየደረሱ መሆኑን ተከትሎ ተጨማሪ የትራፊክ መብራት ለመትከል መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ ለከተማችን በጎ አሳቢ ከሆኑ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ችግሩ በስፋት በሚታይባቸው በአሮጌው ዲፖ ቀበሌ 13 እና አባይ ማዶ ገበያ አካባቢ በሚገኙ 2 ዋና መንገዶች ላይ ሶላር የተገጠመላቸው የትራፊክ መብራቶችን እየገነቡ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ስንታየሁ ገለፃ የተከላ ስራው በቅርብ ቀናት የሚጠናቀቅ ሲሆን በእነዚህ መንገዶች ላይ ይታይ የነበረውን የትራፊክ ፍሰት ምቹ ከማድረግ ባለፈ ካሁን በፊት ይደርስ የነበረውን የሰው ሕይወት ህልፈት፣ የአካል መጉደልና እና የንብረት መውደምን እንደሚቀንስ ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም በሚደረግ ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ የተሽከርካሪ ፍሰት በሚከሰትባቸው መንገዶች ላይ ተጨማሪ የትራፊክ መብራቶች ተከላ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል፡፡