ሐምሌ 02/2013
በአካባቢ ፅዳት፣ ዉበትና የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ እንዲሁም መልሶ የመጠቀም ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተገለፀ፡፡
================================
በባህርዳር ከተማ አስተዳደር አካባቢ ጽዳትና ውበት ጽ/ቤት የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድና መልሶ መጠቀም ቡድን መሪ ወ/ሮ የዉብስራ የሽዋስ ከተማችን በደረቅና ቆሻሻ አወጋገድና አጠቃቀም ዙሪያ አበረታች ተግባራት እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በከተማ አስተዳደሩ ባሉ ሁሉም ክፍለ ከተሞች በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያሉ ደረቅ ቆሻሻዎች በሳምንት አንድ ጊዜ ፣በድርጅቶች እና ተቋማት አካባቢ ደግሞ እንደ ተያዘላቸዉ ዉል መሰረት ማንኛዉም ደረቅ ቆሻሻ የማንሳት ስራ በመሰራት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
በከተማችንን ለብዙ ዓመታት የደረቅ ቆሻሻን ለማስወገድ የነበረዉ የሰዉ ኃይል 6 ማህበራት ብቻ የነበሩ ሲሆን የከተማዋን ስፋት እና እየታዩ የነበሩ የፅዳት መጓደሎችን ግምት ዉስጥ በማስገባት በ2012 ከነበሩ አዳዲስ 8 ማህበራት በተጨማሪ በ2013 ደግሞ 9 ማህበራትን በማደራጀት በአሁኑ ሰዓት 23ቱ በደረቅ ቆሻሻ ፣2ቱ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል እንዲሰሩ በማሰማራት ከተማችን ለኗሪዎቿ ምቹ፣ ፅዱና ማራኪ እንድትሆን ያላሳለሰ ጥረት በመደረግ ላይ አንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
በክፍለ ከተሞች ቤት ለቤት ደረቅ ቆሻሻዎችን ለማንሳት 14 የተደራጁ እና የተመደቡ ማህበራት ሲኖሩ በአስፋልት፣በኮብል እና ተፋሰሶችን ለማፅዳት ደግሞ 9 ማህበራት ተመድበዉ እየሰሩ ከመሆኑ ባለፈ የደረቅ ቆሻሻን በኮምፖስት መልክ አዘጋጅቶ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ደግሞ 2 ማህበራትን በማደራጀት ሁሉም በስራ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
በመሆኑም በከተማችን ለሚገኙ ስራ ፈላጊ ወጣቶች እንዲሁም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ለሚገኙ እማውራና አባውራ ነዋሪዎችን በ25 ማህበራት በማደራጀት ለ1787 ግለሰቦች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ሳታላይት ከተሞች ከላይ የተገለፁ ማህበራት በያዙት ዉል መሰረት በሳምንት 1 ጊዜ የተከማቹ ደረቅ ቆሻሻዎችን በማስወገድ ላይ እንደሚገኙና በቀጣይ ዓመት ሁሉም ሳታላይት ከተሞች የየራሳቸዉን የፅዳት ማህበራት እንዲያቋቋሙ እቅድ የተያዘ መሆኑንም የቡድን መሪዋ አክለዉ ገልፀዋል፡፡