ጂኦግራፊ
መልካም ምድራዊ አቀማመጥ
የባህርዳር ከተማ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከሚገኙት ታላላቅ ከተሞች ውስጥ አንዷ ስትሆን በአጠቃላይ የቆዳ ስፋቱም 42160 ሄክታር ይጠጋል፡፡ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡም 11 ዲ 38 ሴ ሰሜን ላቲቱዩድ እና 38 ዲ10 ሴ ምስራቅ ሎንግቲዩድ መካከል ይገኛል፡፡ ከባህር ጠለል በላይ ያላት ከፍታ 1801 ሜትር ሲሆን ከተማዋ በጣና ሐይቅ ደቡባዊ ጫፍ ላይ የምትገኝና የጥቁር ዐባይ ወንዝ አቋርጧት ረጅሙን ጉዞ የሚጀምርበት በመሆኑ ልዩ ማራኪና ግርማ ሞገስ የተላበሰ የተፈጥሮ ገጽታ ተሰጥቷታል፡፡ ባህርዳርን በምስራቅ ተንታ፣ በደቡብ ሰባታሚት፣ በሰሜን ጣና ሃይቅና ወንጀጣ ቀበሌ እንዲሁም በምዕራብ ይባብ እየሱስ ያዋስኗታል፡፡ ከአዲስ አበባ በሰሜን አቅጣጫ 565 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ስትገኝ በውስጧ ካላት የቱሪዝም ሃብት በተጨማሪ የሰሜን ኢትዮጵያ ቱሪስት መስህቦች ቀለበት (Northern Ethiopia historic route of movments) ዋነኛ ማዕከል ነች፡፡ ከተማዋ ተፈጥሮአዊ እምቅ የቱሪዝም ሃብት ያላት ከተማ ናት፡፡